የጠቅላይ ሚኒስትሩን “ወደ ሀገር ቤት እንግባ” ጥሪ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አጋር ሆኖ ያስተባብራል

ህዳር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን “ወደ ሀገር ቤት እንግባ” ጥሪ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አጋር ሆኖ ለማስተባበር ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት በመግባት በዓላቶችን እንዲያከብሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

የአውሮፓዊያኑን አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ለማክበር 1 ሚሊዮን ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የቀረበውን ጥሪ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አጋር ሆኖ ለማስተባበር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የቀረበውን ግብዣ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

ዳያስፖራው ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ለማዘመን የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ምክር ቤቱ አመልክቷል።

አሸባሪው ህወሓት ከውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስና ሀገር ለማዳን በሚደረገው ትግል በመሳተፍ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል አጋር ሆኖ ለማስተባበር ዝግጁ እንደሆነም አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአውደ ግንባር እየመሩት ባለው “ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” የኢትዮጵያ አሸናፊነት ይረጋገጣል ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎና ድል መኩራቱን ገልጿል።

ዳያስፖራው በሚገኝባቸው ሀገራት ሁሉ በሰላማዊ ሰልፍና በዲፕሎማሲ ዘመቻ የዜግነት ድርሻውን በመወጣት ከመንግስት ጎን መሆኑን እያሳየ መሆኑን ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስና ሰላም ለማረጋገጥ የመንግስትን ጥሪ ተቀብሎ ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል።

በመጪው ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም 1 ሚሊየን ሰዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ በመንግስት በኩል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

Leave a Reply